በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ቀጨኔ አካባቢ የሚኖሩ አስታራቂ እናቶች በእራስ ተነሳሽነት በተለያዩ ምክንያቶች የተጋጩ የአካባቢው ነዋሪዎችን ማስታረቃቸው ለዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ገለፁ፡፡
ቁጥራቸው አምስት በጎ ፈቃደኛ እናቶች በአካባቢው ለዘመናት በህብረተሰብ ውስጥ የነበሩ ግጭቶች አለመግባባቶችና ቂምና ጥላቻን ለማስወገድ እየሰሩ መሆኑ አብራርተዋል፡፡ እናቶች ግጭቶች ከህግ በፊት በአካባቢ ሽማግሌዎች መፍታት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን በመረዳት ለበርካታ ዓመታት በቂም ጥላቻ እና ግጭት ውስጥ የነበሩ 250 የአካባቢው ሰዎች ይቅር በማባባል በሰላም እንዲኖሩ አስችለዋል፡፡ የእርቅ ሂደቱ የአካባቢውን ባህልና እምነት መሰረት በማድረግ ‹‹ይቅር ማለት ለፈጣሪ ነው፤ ይቅር ባይነትም ታላቅነት ነው ›› በማለት የተጋጩ ግለሰቦች፣ ቤተሰቦች እና ድንበርተኞችን ይቅር እንዲባባሉና በሰላም እንኖሩ ማስቻላቸውን አብራርተዋል፡፡ ከተቋቋሙ ሁለት ወራት የስቆጠሩት እነኚህ በጎ ፈቃደኛ አስታራቂ እናቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተቀባይነትና ተምሳሌታዊነት በመጠቀም እስካሁን የአካሄዷቸው የይቅርታና የማስታረቅ ስራዎቻቸውን ወደፊትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል፡፡ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አባል የሆኑት የጥበብ ሰው ደበበ እሸቱ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት እንዲህ ያለው የአስታራቂ እናቶች ማህበረሰብ ተኮር ይቅርታና የእርቅ ስነስርአት በእጅጉ የሚደነቅና የሚበረታታ በመሆኑ እናቶች እያደረጉ ያሉት ወደ ሌሎች አካባቢዎች ቢሸጋገር ሀገራዊ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡ የዕርቀ ሠላም ኮሚሽን ሕብረተሰቡ በዕርቅና በሠላም ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ የተለያዩ ዕቅዶችን ነድፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን ዕቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ‘ቲክቫህ ኢትዮጲያ’ ከሚባል የቴሌ ግራም ቻናል ጋር በመተባበር ወጣቱን አሳታፊ የሆነ ፕሮጀክት ይፋ አድርገዋል፡፡ በርካታ ተከታዮች ያሉት ቻናሉ ወጣቱ በተለያዩ መስክ ያለውን እምቅ ችሎታ ተጠቀሞ በየአካባቢያቸዉ ያለዉን ሰላምንና ዕርቅን ማስፈን ሚችሉ ሀገር በቀል እዉቀቶችንና የዕርቅ አፈታት ስርዓቶችን እንዲለዩና ለሌላዉ ማህበረሰብ ክፍል እንዲያሳዉቁ የሚያስችል ነዉ፡፡
|